የመስከረም ጥቢ ዋዜማ በሆነበት ወቅት ሁሉ በየዓመቱ ልጆች ወንዶቹ ከሆያ ሆዬ ጭፈራ ናፍቆት አንሥቶ የአበባ ሥዕላዊ ንድፍ ግዥና የዕንቁጣጣሽን ‹‹እንኳን አደረስዎ›› ገጸ በረከት እያዘጋጁ መሰንበታቸው ይታወቃል፡፡ ሴቶች ደግሞ በዚያው መስከረም መጀመሪያ ቀን በሚውለው የዘመን መለወጫ በዓል ዕለት ከእነ ማን ጋር እየዞሩ ‹‹አበባዬ ሆይ›› በማለት ብሥራተ ዘመኑን በዘፈን በዝማሬ ‹‹ የምሥራች›› ይሉ ዘንድ የሚበቁበትን ሁኔታ እያሰላሰሉ የቀኑን ፈጥኖ መድረስ በጉጉት መጠባበቃቸው እሙን ነው፡፡
ልጆች ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ በጥቅሉ ዕንቁጣጣሽን ገና ከነሐሴ ወር መባቻ አንሥቶ ብሩኅ ተስፋ ሰንቀው፣ ክፉኛ ናፍቀው የትውስታን እውነታ በስሜታዊ ትዝታ በዓይነ ሕሊና ያዩታል፡፡ ይህ በየዓመቱ ያው ‹‹የተለመደ›› ቢባልም ‹‹ሰርክ አዲስ›› ኩነት ነው፡፡
ልጆች የዚህን ያህል ደስ ብሏቸው የቀኑን መድረስ በጉጉት ይጠባበቃሉ፡፡ የአዲስ አበባችን ወላጆች ግን በአፍራሻው የትምህርት ቤቱን ፍለጋ ይያያዙታል፡፡ በተለይ ትናንሽ ልጆችን በግል ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ እዚህም እዚያም የሚሯሯጡ ወላጆች እንደ ድሮ የመመዝገቢያውን ተመን የየወሩን ክፍያ መጠን ከአቅም ጋር እያነጻጸሩ ፣ አንዱን ከሌላው እያወዳደሩ የሚመክሩበት ሁኔታ ብቻ አይደለም የሚስተዋለው፡፡ የወላጆች የዘመኑ ትልቅ ጉዳይ ትምህርት ቤቱ ያለበትን አካባቢ በውስጥ አወቅ ነዋሪ እያስተነተኑ የመረዳትም ነገር አለበት፡፡
ድሮ ቢሆን ‹‹ስንት ይከፈላል? አከፋፈሉስ በየወሩ ነው ወይስ በየክፍለ ዘመነ ትምህርቱ፣ ወይስ በቅድሚያ በየዓመቱ ሙሉ ክፍያ ይጠይቃል?›› ወዘተ፣ እየተባለ ይጠና ነበረ፡፡ ዛሬ ግን ሌሎችንም ዓበይት ጥያቄዎች ይጨምራል፡፡
‹‹ትምህርት ቤቱ ያለበት ወይም የተከራየበት ስፍራ ምን ይመስላል? ›› የሚለውን ጥያቄ ‹‹ በቁጥር 1›› ያስቀምጣል፡፡ ይህ ሲባል ግን ትምህርት ቤቱ ተቆርቁሮ ተግባር የጀመረበት ቦታ ዙሪያ ‹‹ የሚያነሣው አጥቶ በማዳበሪያ የተቋጠረ ፣አልያም አለማዳበሪያ የተከመረ ደረቅ ቆሻሻ አለ ወይ? ›› የሚለው ተገቢ ምላሽ ያጣ ጥያቄ ማለት አይደለም፡፡ በርግጥ እርሱም ከተነሣ በጣም ድንቅ ጥያቄ በሆነ ነበር፡፡ ስለ እርሱ በየመገናኛ ብዙኃኑ አማካኝነት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ብዙ ብዙ እየተወተወተ ‹‹ታሪክ›› ወደ መሆን አዝማሚያ የሚያመራ ይመስላል፡፡
ነገር በነገር መነሣቱ አይቀርምና ‹‹አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት›› በምሕጻረ ቃሉ ‹‹አተት›› ወደ ‹‹መተት›› ‹‹ (መደበኛ ተቅማጥና ትውከት) ተለውጦ የለ እንዴ ! ››እየተባለ የመሸታ ቤት መሳለቂያ ከሆነ ሰንበትበት ማለቱ እጅግ የሚያሳዝን መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በአሳዛኝ መልኩ ይህን እያደመጥን መስከረም ሊጠባ ዳር ዳር ብሏል፡፡
ወደ ትምህርት ቤቱ አድራሻ ስመለስ የወላጅ ጥያቄዎች ‹‹ በአካባቢው ያሉ የጫት ቤቶች የሌላም ዕፅዋት ሽያጭ መደብሮች፣ የመሸታ ቤቶች ...ሁኔታ እንዴት ነው ስንት ናቸው…›› የሚሉት ሆነው ነው የተገኙት፡፡
ምናልባት እነዚህ ጥያቄዎች ለዋዘኞች በውኑም እንደ ዋዛ ታይተው ሊታለፉ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ፈጽሞ አይደሉም፡፡ መቼም መች ‹‹ ድሮ በእኛ ዘመን›› ብል የሚከፋ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ቢኖርም ይቅር ባይነቱን እንደ ማይነፍገኝ ተማምኜ እቀጥላለሁ፡፡
እኛ ሸበቶዎች በነበርንበት ዘመን አንዳንድ የሻይ ቤቶች እንኳ በትምህርት ቤት አካባቢ የግዳቸውን ተንገዳግደው ቢያስፈቅዱም ‹‹ልጄ ፓስቴ ይለምድብኛል ፣የሲጋራ ሱሰኛ ይሆንብኛል፣ሌብነት ይማርብኛል…›› በማለት ወላጆች ጠዋት ማታ ወደ ፈቃድ ሰጭው የያኔ ‹‹ማዘጋጃ ቤት›› እየሄዱ በመጮህ እስከ ማዘጋት የደረሱ እንደነበሩ በግሌ እኔ በሚገባ አስታውሳለሁ፡፡
መቼም መች ያንኑ ‹‹ በተለምዶ›› የሚለውን አነጋገር እኔም እጠቀምበት ዘንድ ሁኔታዎች ያስገድዱኛልና በተለምዶ ልዑል መኮንን ት/ቤት፣ በተለምዶ አስፋ ወሰን ት/ቤት በተለምዶ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ... ይባሉ የነበሩ ለዚህ ዓይነተኛ ምስክሮችም ናቸው፡፡
ዛሬ ግን ከአንድ የግልም ሆነ የመንግሥት ወይም የሕዝብ ት/ቤት አካባቢ ደጃፍ ብዙ ሳይርቅ የጫት ቤቱ፣ የዳንስ ቤቱ፣ የመጠጥ መደብሩ፣ ወዘተ ተበራክቶ ይገኛል፡፡ ከዚህም በላይ ሳምቡሳ ሻጩ፣ቺፕስ አንፋሪው፣የሲጋራው ‹‹ሱቅ በደረቴ››ው ገና ደወሉ ሲደወል ደጃፍ እየተጋፉ ይታያሉ፡፡
እንዲያውም አንዳንዱን ባለ መደብር ‹‹ ለመሆኑ እናንተ ምን ይሰማችኋል? እንዲህስ ስታደርጉ ምን ስሜት ይሰጣችኋል?›› ብዬ ብጠይቀው የሰጠኝ መልስ አይረሳኝም፡፡
አንዱ ‹‹ታዲያ የት እንሂድ? .አሁን እርስዎ ቦታ ስጡን ብልዎት ይሰጡኛል? ቢሰጡኝስ ምን ያደርግልኛል?›› ሲለኝ ሌላው ደግሞ ‹‹ ትምህርት ቤት ቀለም ይመግባል እኛ ደግሞ የያዘው ቀለም እንዳይለቅ ማስቲቻቸውን እናቀርባለን›› ብሎ አሹፎብኛል፡፡
በዛሬ ጊዜ እንደ ጥንቱ ሁሉን ነገር ወደ ማዘጋጃ ቤት ሄዶ እየጮሁ ሰሚ የሚታጣበት ወቅት አይደለም፡፡ እንደ ድሮው የኛ ዘመን ሕዝብ ለአስተዳደር ፍጹም ባይተዋር የሆነበት ጊዜ አይደለም፡፡ ሕዝብ በየወረዳው እየተሳተፈ፣በመረጠው ተወካይ አማካኝነትም ሆነ ራሱ በነዋሪነቱ ችግሩን እያስመረመረ መፍትሔ ማግኘት የሚቻልበት ሥርዓት ይዘናል፡፡ ይህ የማይታበል ጥሬ ሐቅ ነው፡፡
እናስ የዛሬዎቹ የአዲስ አበባችን ወረዳዎች ለዚህ ቁጥጥር ሳይበቁ ቀርተው ነው የምግባረ ብልሹነት ምንጭ የሆኑ መደብሮች በምግባረ ሠናይ አጥር ዙሪያ እንደ አሸን የፈሉት? አንዱ ለአቅም ግንባታ ሌላው ለአቅም ፍንካታ እኩል ይሰለፉ ዘንድ መፍቀድ ምን ይባላል? አንዱ ሲሠራ ሌላው ሲያፈርስ ፣አንዱ ሲያንጽ ሌላው ሲገረስስ ይስተዋል ዘንድ መመልከትስ ምንድን ነው?
አንዳንድ «ነጋዴ ነን›› ባዮች ስለ ‹‹ነጻ ገበያ›› በየመሸታ ቤቱ መድረክ ከፍተው በሰፊው ሲደሰኩሩ ይሰማሉ፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሁለት የሆኑ ደንብ አስከባሪዎች ‹‹የጫት መሸጫ መደብሮች መቃሚያ ሊሆኑ እንደማይገባ›› አስጠንቅቀው በመሄዳቸው ብቻ ቃሚውም፣ አስቃሚውም በአንድ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ባለው አንድ መሸታ ቤት ተሰብስበው ጉዳዩን ‹‹ በአግራሞት›› ሲተርኩ የሰማ ሰው እንዳጫወተኝ ያን ‹‹ነጻ ገበያ›› ለአረቄ ማሟሻ አድርገው ብዙዎችን አስቀዋል፡፡
‹‹ነጻ ገበያ›› ሲባል ሰዎች ‹‹ ለአንዳንዶች›› ይላሉ እንጂ ለበርካቶች ገና በባይተዋርነት ያለ ወይም በብዙዎች ታውቆ የተናቀ ነገር ይመስለኛል፡፡ እውን ምግባር ስንኩልነት ከነጻነት ተርታ ገብቶ ይቆጠራል ማለት የሚቻልት አገር አለ?
ወረደም ወጣ፣ ግራም ነፈሰ ቀኝ ትምህርት ቤቶች ያሉበት አካባቢ ስላሉ የንግድ ቤቶች ወይም በተቃራኒው ንግድ ቤቶቹ በቅድሚያ ለዘመናት ስፍራውን ይዘውት ኖረው ከሆነ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሚቆጣጠረው የየወረዳው የትምህርት ጽ/ቤት እንዲህ ዓይነቶቹ ተግባራት በአንድነት ግራና ቀኝ ሆነው የሚራመዱበት አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ መመርመርና ተገቢውን ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ይህ በየጊዜው ሲነገር የኖረ ሰሚ ያጣ አቤቱታ ይመስለኛል፡፡ ተገቢው ቁጥጥር እና ማናቸውም ርምጃ መወሰድ ምንም አማራጭ ሊኖረው የማይችል ጉዳይ ነው፡፡
አለበለዚያ ያ ሰው ያለው ነገር ሊሆን ነው፡፡ ይኸውም ‹‹ልጄን አድርስልኝ›› ተብሎ የተነገረው አንድ ሰው ቦታውን ባለማወቁ ‹‹የት ነው ? ›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ እዚያ ‹‹ የእገሌ ጫት ቤት ብለህ ብትጠይቅ ታገኘዋለህ›› አለው ይባላል፡፡ ይህ መልካም መታወቂያ አይመስለኝም፡፡
በሰላም ያገናኘን
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ