2016 ኦክቶበር 20, ሐሙስ

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከኮማንድ ፖስት የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ አፈፃፀም መመሪያ

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበርና የሕዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 28 ቀን 2009 .ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን፤ በቅርቡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተስተዋለውን የጸጥታ መደፍረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር አድርጎ የሕዝቡን ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት ለመመለስ በየቦታው ለታየው ሁከት፣ ረብሻና ሥርዓት አልበኝነት ዋንኛ መገለጫ በሆኑ አውዳሚ ተግባራት ላይ የተጣለውን ክልከላ እንዲሁም ክልከላዎቹ ሲጣሱ በአዋጁ መሠረት የሚወሰዱ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን በመለየት አስቀድሞ ለሕዝብ ማሳወቅ እንዲሁም አዋጁ ተፈፃሚ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ክልከላዎቹን ጥሰው በሚገኙ ሰዎችና ድርጅቶች ላይ ተገቢውን የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ሆኖ ስለተገኘ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር---መስከረም 28/2009 አንቀፅ 13/2/ እና በደንቡ አንቀፅ በተፈቀደው መሠረት የሚከተለው መመሪያ ወጥቷል።
በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የተከለከሉ ተግባራት
አንቀፅ 1. ሁከትና ብጥብጥ የሚያስነሳ ቅስቀሳና ግንኙነት ማድረግ
ማንኛውም ሁከት፣ ብጥብጥና በሕዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃር የሚፈጥር፣
ይፋዊም ሆነ ድብቅ ቅስቀሳ በማናቸውም መልኩና ዘዴ ማድረግ፣ ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ ማተምና ማሰራጨት፣ ትዕይንት ማሳየት፣ በምልክት መግለፅ ወይም መልዕክትን በማናቸውም ሌላ መንገድ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፣ ፍቃድ ሳይኖር ማንኛውንም ህትመት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ወይም ወደ ውጭ ሀገር መላክ፤መልዕክት በኢንተርኔት፣ በሞባይል፣ በጽሑፍ፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በማህበራዊ ሚድያ ወይም ሌሎች የግንኙነት ዘዴዎች መለዋወጥ።
አንቀፅ 2. ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ
በሽብር ከተሰየሙ ድርጅቶች እና ከፀረ ሰላም ቡድኖች ጋር ማናቸውንም ግንኙነት ማድረግ፣ የአሽባሪ ድርጅቶችን የተለያዩ ጽሑፎች መያዝ ማሰራጨት፣ አርማቸውን መያዝ ወይም ማስተዋወቅ፣የቴሌቪዥን ወይም የሬድዮ ፕሮግ ራምን መከታተል፣ የኢሳት፣ የኦ.ኤም.ኤንእና የመሳሰሉትን የሽብርተኛ ድርጅቶች ሚዲያዎችን ማሳየት፣ መከታተልና ሪፖርት ማድረግ የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 3. ያልተፈቀደ ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ
የሕዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል ከኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ ውጪ ማናቸውም ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 4. ለሕዝብ አገልግሎት አለመስጠት
(1) ሕዝብ የሚጠቀምባቸውን ወይም ፈቃድ የወጣባቸው የንግድ ሥራዎች፣ ሱቆች ወይም የመንግሥት ተቋማት መዝጋት ወይም ምርትና አገልግሎት ማቋረጥ፣ ከሥራ ቦታ ያለ በቂ ምክንያት መጥፋት ወይም ሥራ ማቆም፣ ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት፣ ሥራን መበደል፣
(2) የመንግሥት ወይም የግል ተቋማት ሠራተኞች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዳይገቡ መዛትና ማስፈራራት የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 5. በትምህርት ተቋማት አድማ ማድረግ
በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች እና በሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደትን የሚያውክ አድማ ማድረግ፣ የትምህርት ተቋማትን መዝጋት ወይም በእነዚህ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረግ የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 6. በስፖርት ማዘውተሪያዎች አድማ ማድረግ
በስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆኑ ሁከቶችን፣ ብጥብጦችን መፍጠር የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 7. የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ማወክ
የተሽከርካሪ፣ የእግረኛ እና ሌሎች የመጓጓዣ ዘዴዎችን እንቅስቃሴ መንገድ በመዝጋት በዛቻ እና በሌሎች መሰል ድርጊቶች ሰላማዊ እንቅስቃሴን ማወክ፣ አገልግሎት ማስተጓጎል፣ የመጓጓዣ ዋጋ ታሪፍ መጨመር፣ የሚመለከተው አካል ከደለደለው የሥራ ስምሪት ውጪ መሆን የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 8.በመሠረተ ልማቶችና ሃይማኖታዊ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረስ
በግል፣ በሕዝብና በመንግሥት ማናቸውም ተቋማት፣ በመሠረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች የልማት አውታሮች እንዲሁም በሃይማኖታዊ ተቋማት ላይ በማንኛውም መንገድ ጉዳት ማድረስ ወይም ዘረፋ መፈጸም የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 9. ሕዝባዊና ብሔራዊ በዓላትን ማወክ
ሕዝባዊና ብሔራዊ በዓላትን በማንኛውም ሁኔታ ማወክ፣ ማደናቀፍ ወይም ከበዓሉ አላማ ጋር የማይገናኙ የፖለቲካ አጀንዳዎች ወይም መፈክሮችን በማንኛውም መንገድ ማስተጋባት የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 10. ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሕዝባዊ በዓላት ላይ ቅስቀሳ ማድረግ
ሃይማኖታዊ ተቋማት ውስጥ በሚደረጉ ስብከቶችና ትምህርቶች ሃይማኖታዊ አስተምህሮት ከማድረግ ውጪ በሕዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃርን የሚፈጥር፣ በኅብረተሰቡ ላይ ስጋት የሚፈጥር፣ ሁከትና ብጥብጥ የሚቀሰቅስ ቅስቀሳ ማድረግ የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 11. የሕግ አስከባሪዎችን ሥራ ማወክ
የሕግ አስከባሪ አካላት የሚሰጡትን ማንኛውም ትዕዛዝ አለማክበር ሥራቸውን ማደናቀፍ፣ ለፍተሻ አለመተባበር ወይም እንዲቆም ሲጠየቅ አለማቆም፣ ኬላዎችን ጥሶ ማለፍ የተከለከለ ነው፣
በሕግ አስከባሪ አካላት ባልደረቦች ላይ ጥቃት መፈጸም ወይም ለመፈጸም መሞከር የተከለከለ ነው፣
አንቀፅ 12. ያልተፈቀደ አልባሳት መልበስ
የሕግ አስከባሪ ኃይሎችን ዩኒፎርም መልበስ፣ ይዞ መገኘት፣ በቤት ማስቀመጥ፣ አሳልፎ መስጠትና መሸጥ ክልክል ነው።
አንቀፅ 13. የጦር መሣሪያ ይዞ መግባት
ማናቸውም የጦር መሣሪያ፣ ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ወደ ገበያ፣ ሃይማኖት ተቋማት፣ ሕዝባዊ በዓላት የሚከበሩበት ወይም ወደ ማናቸውም ሕዝብ የሚሰበሰብበት ቦታ ይዞ መግባት የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 14. ትጥቅን በሦስተኛ ሰው እጅ እንዲገባ ማድረግ
ማንኛውም የሕግ አስከባሪ አካላት ባልደረባ ወይም ማንኛውም ሕጋዊ ትጥቅ ያለው ሰው ትጥቁን በማንኛውም ሁኔታ በሦስተኛ ሰው እጅ እንዲገባ ማድረግ ክልክል ነው።
አንቀፅ 15. መቻቻልን እና አንድነትን የሚጎዳ ተግባር መፈጸም
ማንነትን ወይም ዘርን መሠረት ያደረገ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት መፈጸም ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ንግግር መናገር የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 16. የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ደህንነት፣ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት የሚጎዳ ተግባር መፈጸም
ማንኛውም ሰው ከውጭ መንግሥታትም ሆነ ከውጭ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር የሀገር ሉአላዊነት፣ ደህንነትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ሊጎዳ የሚችል ግንኙነትና የመልዕክት ልውውጥ ማድረግ የተከለከለ ነው፣
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የሀገርን ሉአላዊነት፣ ደህንነት እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ማናቸውም ጋዜጣዊ መግለጫ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ሚዲያዎች መስጠት ክልክል ነው።
አንቀፅ 17. ያልተፈቀደ ቦታ መገኘት
ከስደተኛ ካምፕ አግባብ ካለው አካል ከሚሰጥ ፈቃድ ውጪ መውጣት ወይም ሕጋዊ ቪዛ ሳይኖረው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 18. ያለፈቃድ ስለሚደረግ የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ
የኮማንድ ፖስቱን እውቅናና ፈቃድ ሳያገኙ ዲፕሎማቶች ለራሳቸው ደህንነት ጥበቃ ሲባል ከአዲስ አበባ ከአርባ (40) ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውጪ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 19. የሕግ አስከባሪ አካላት ግዳጅ ላይ ስለመገኘት
ማንኛውም የሕግ አስከባሪ አካል ባልደረባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈፃሚ በሚሆንበት ጊዜ ከሥራ መልቀቅ ወይም አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር የዓመት እረፍት ፍቃድ መውሰድ ክልክል ነው።
አንቀፅ 20. የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ ድጋፍ ማድረግ
በዚህ መመሪያ የተከለከሉ ተግባራትን በመተላለፍ ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ መደገፍ እንዲሁም ከለላ መስጠት፣ መደለያ መስጠት፣ ማበረታታት የተከለከለ ነው።
በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዳይፈጸሙ የተከለከሉ ተግባራት
ከላይ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ከአንቀፅ 21-24 የተዘረዘሩት ክልከላዎች ኮማንድ ፖስቱ እየወሰነ ይፋ በሚያደርጋቸው ቦታዎች ወይም አካባቢዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ።
አንቀፅ 21. የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ
ማናቸውም የጦር መሣሪያ፣ ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ከግቢውና ይዞታው ውጪ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
አንቀፅ 22. በልማት አውታሮችና መሠረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት
የኢኮኖሚ አውታሮች፣ መሠረት ልማትና የኢንቨስትመንት ተቋማት፣ የእርሻ ልማቶች፣ በፋብሪካዎች እና በመሰል ተቋማት አካባቢ ከቀኑ 12 ሰዓት በኋላ እስከ ንጋት 12ሰዓት ድረስ ከተፈቀደለት ሠራተኛ በስተቀር ማንኛውም ሌላ ሰው መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፣
ከላይ በተመለከቱት ቦታዎች የሰዓት እላፊውን ተላልፎ በተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ የጥበቃ ወይንም የሕግ አስከባሪ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ