ሐሙስ 20 ኦክቶበር 2016

አገር ማለት...

በድቅድቅ ጨለማ በፒያሳ ምድር እየተጓ ዝኩ ነው። ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ ማየት ስለሚያስፈራ በማይታየኝ መንገድ በግምት እያማተርኩ እከንፋለሁ። ጨለማው እንዴት ያስፈራል! አልፎ አልፎ መንገድ ዳር ተቀምጠው ሽቅብ የሚገረምሙ ልጆች ይታያሉ። እነርሱን ካልመሰልኩ ጉዳት እንደሚያደርሱብኝ ስለገባኝ በተቻለኝ አቅም ደንታ ቢስ መስያለሁ። ከኋላ ሁለት ወጣቶች እንደተከተሉኝ ሲገባኝ ቆም ብዬ አሳለፍኳቸው በፍርሃት ውስጥ ሆኜ።
ምን እንደሚመጣ እየገመቱ ከነፍስ ጋር ግብግብ፤ ግቢ ነፍስ፤ ውጪ ነፍስ። ይሁን እንጂ አላማ ላለው ሰው ምንም አይደለም። ጉዞዬን ያገባደድኩት ወጣቶች ተሰባስበው ከሚጫ ወቱበት ቦታ ስደርስ ነው። ሁሉም በራሱ ምህዋር ይሽከረከራል። እነርሱን ባልመስልም ተመሳስየ ተቀመጥኩ። በቤቱ የተለያየ ወሬ ይነፍሳል፤ ቀርቤ ለማድመጥ ስሞክር ስለ አገር ነበር የሚያወሩት። አገር በስካር መንፈስ ምን ትመስል ይሆንብዬ ጆሮዬን ለእነሱ ተውኩላቸው። «ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል» እንዳይሆን ብሰጋም ማድመጤን ተያያዝኩት፡፡
‹‹እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ አገር ለእናንተ ማን ነውትመልሱልኛላችሁ?›› በማለት ጥሩ የለበሰና ቂቅ ያለ ሰውዬ ጥያቄውን አስከተለ።
«ቀላል ነው፤ ይህን ለመመለስ ብዙ ማውራት አይጠበቅም። እንግዲህ ስለ አገር ብዙ ተዘፍኗል፣ ብዙ ተገጥሟል፣ ብዙ ብዙ ተጽፉል፣ ተነግሯልም፣ ተብሏልም። አይደል እንዴ?›› ሲል አንድ እጁን ከፍ ዝቅ እያደረገ ለማስረዳት የሚሞክር ሰው፤ በስካር መንፈስ መሆኑ ግን ንግግሩ ያሳብቅበታል፤ ቀጠለ፥
«እንደዚህ ተሸቀርቅረን ዘና የምንል በአገራችን በመሆናችን አይደልታዲያ አገርን ከእኔው ከራሴ ውጪ ማን ይገልጻታልሁላችሁም ወደኔ ተመልከቱ፤ ወደራሳችሁም ተመልከቱ አገር ማን መሆኑ ይገባችኋል›› ሲል ሁሉም ሳቁበት፡፡
‹‹ታዲያ የአገር ትርጉሙ አልገባሽማቢገባሽ እያንዳንድሽ አትስቂም ነበር። ታዲያ አገር ምንድን ነው እኔ አገር ካልሆንኩ?» አለ ጥያቄውን ወደ ሌሎቹ እየተወ፡፡
‹‹ሁላችሁም አልገባችሁም፤ በአሁኑ ወቅት አንታርክቲክም አገር ነው!›› አለ በእጁ የያዘውን ሜታ ጭልጥ እያደረገአይኖቹ እየተን ጮለጮሉ፡፡
‹‹እንዴት ሆኖ አንታርክቲክ አህጉር እንጂ አገር ሊሆን ቻለየበረዶ ክምር እንጂ ምን የያዘ መሰለህነው በቅጡ አታውቀውም። ለነገሩ አልፈርድብህም ንድፈ-ሃሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ ትምህርት ቀስመህ አንታርክቲክ አገር ነው ብትል አይደንቅም። እኔ እምልህ ጂኦግራፊ ትምህርት ቀረ እንዴማፕ ሪዲንግ አትማሩም?›› በፊት ሲመልስ የነበረው ሃሳቡ ስላበሳጨው ነው መሰል የጥያቄ መዓት አወረደበት፡፡
‹‹አልገባሽም ነጮበፊት በፊት ነጭነት ስልጣኔ ነበር። የአንድን ሰው ብልጠት ለመግለጽ እንኳ እሱ «እንግሊዝ ነው» እንል ነበር። እድሜ ለፓን አፍሪካኒዝም ዘማሪዎች ጥቁርነትም ብልጠት ሆነ። ቀደምት የእኛ አያቶች በጥቁርነታቸው ተሸማቀውና አንገት ደፍተው የባርነት ቀንበር በተሸከሙበት ወቅት ጥቁርነት ሞኝነት ነበር። ነጭነት ደግሞ ብልጠት። ነገሩ ግልጽ የሆነው ነጭነትና ጥቁርነት የቆዳ ቀለም መሆኑን የአፍሪካ ምሁራን ሞግተው ሲያሸንፉና አፍሪካን የራሳቸው ሲያደርጓት ነው። ጉዳዩ ይህም አይደለም። ሰው አገር ካልሆነ አገር ሰው ስለሚሆን እንጂለነገሩ አይገባህም። ለመሆኑ የምሁሩን ታሪክ ታውቀዋለህ?›› አለው በነገር ሸንቆጥ እያደረገ። ሙግታቸው ስላስደሰተኝ ይበልጥ ቀረብኳቸው።
‹‹የትኛው ምሁር ብዙ ምሁሮች አሉ?›› ብሎ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት።
‹‹ከእብዶች መሃል ጤነኛ ሆኖ ስተለገኘው ምሁር።›› አለው በተራው እየተጎነጨ
‹‹ምሁር ስለሆነ አበደ ይሆን?›› አለው ሳቅ ብሎ፤
‹‹በጣም የተመራመረ ምሁር ነበር። ይህ ምሁር በአንድ አነስተኛ የገጠር መንደር ሲኖር የመንደሩ ሰው የሚጠቀምበት የወንዝ ውሃ ላይ ባደረገው ምርምር ውሃው የተበከለ ሆኖ ያገኘዋል። በዚያን ወቅት የመንደሩን ሰዎች ሰብስቦ «ከዚህ ወንዝ አትጠቀሙ ውሃው የተበከለ ስለሆነ ይጨርሳችኋል» የሚል ሃሳብ ያቀርባል። በዚያን ወቅት ነዋሪው «ይህ ሰው የሚለውን አያውቅም፤ ለስንት ዘመናት ስንጠቀምበት የኖርነውን የወንዝ ውሃ ገና ተምሬያለሁ ብሎ መርዝ ነው ይለናል። እርሱ ምሁር ሳይሆን እብድ ነው» በማለት ያገሉታል፡፡ ምሁሩም ከዚያን ቀን ጀምሮ መጠጣቱን ያቆምና የሚሆነውን ሲጠባበቅ የከተማው ሰው ሁሉ ታመመ። እና ይህ እስኪሆን ድረስ አይደለም ማወቅ ማለት፤ ማወቅ ማለት ቶሎ መረዳት ይመስለኛል።›› አለኝ።
‹‹እና አንታርክቲክ አገር ነው እንድንል ነው ይህ ሁሉ ምሳሌ?›› ብሎ ሃሳቡን ጠየቀው፤
‹‹ምድረ-በዳ እንኳ ቢሆን ሰው አገር መሆን ካልቻለ አገር ሰው ለምን አይሆንምለመሆኑ አገር ላንተ ምንህ ነው?›› በማለት ሙግቱን ቀጠለ፡፡
‹‹አገር ማለት ሰው ነው፤ የሰው ዘር የሌለበት ምድረ-በዳና የበረዶ ክምር የተቆለለበት አህጉር በምንም መልኩ አገር ሊሆን አይችልም። አገር እኮ ተራራው፣ ወንዙ፣ ሸንተረሩ፣ ተረተሩ፣ ሸለቆው፣ መንገዱ፣ ፎቁ፣ ፍብሪካው፣ ወዘተረፈ ሳይሆን ሰው ነው›› ብሎ መለሰለት።
‹‹እርግጥ ነው፡፡ ግን እሱ ሊሆን የሚችለው የዘረዘርካቸው ነገሮች የሰውን ልጅ ካልበለጡ ብቻ ነው። እውነታው ግን የሰው ልጅ በተዘረዘሩት ነገሮች ተበልጧል። አንተ አገሬ ነች ብለህ የምትኮራው በምኑ ነውሰው ስደትን ለምን የሚጠላ ይመስልሃልስለማይመቸው እንዳይመስልህ ስደትም ከአገር በተሻለ ሁኔታ ሊመች ይችላል። ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው አገሬውን ካከበሩ ብቻ ነው። እንደ ባላገር ልኮራ የምችለው አገሬ በመሆኗ ስከበርባት ነው። ጃንሆይ ‹ባላገር› ናችሁ እያሉ ስንቱን ጢሰኛ ነው የበዘበዙት። ባላገር መባል ይህ ከሆነ አንታርክቲክ አገር ነው። ባላገር መባል ሳይሆን ባለቤትነትን ማረጋገጥ ከሆነ አንታርክቲክ አህጉር ይሆናል። አስበኸዋልእንደዚህ እስክትጦዝ መጠጣት ባላገርነት አይደለም። ባላገርነት ቤት አልባነት አይደለም። ባላገርነት ልብን ነፍቶ መናገር ብቻ አይደለም፤ ተጠቃሚ መሆንንም ይፈጥራል፤ ይፈቅዳል፡፡ ጢምቢራህ እስኪዞር የምትጠጣው ደስተኛ ሆነህ ይሆን?›› ሙግታ ቸው የቤቱን ቀልብ ስቦታል። ከሙግታቸው ጋር አብሮ የሚሄድ ለስላሳ ሙዚቃ ተለቆ ሁሉም የሁለቱን ሙግት እያደመጠ መብራት ድርግም ሲል ‹‹ኬረዳሽ!! ሳምንት እንቀጥል›› ብለው ተለያዩ።
***
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/environment/item/5585-2016-02-10-16-06-39

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ