‹‹ የዘመን አዲስ አለው ? ›› በሚል ርዕስ ጋዜጠኛ ግርማ ቦጋለ ግንቦት 4ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያወጡት ጽሑፍ በእጅጉ የጠለቀ አተያይና አመለካከት ያዘለ ነው፡፡ የወየበና ያረጀ ዘመን ላይ በአዲስነት ስም መጥቶ የሚደረበው ዘመን ‹‹ራሱን እያከለና እየጨመረ መሄዱ እንጂ አዲስነቱ አልታይህ አለኝ›› በማለት ጀምረው ሃሳቡን ሲያጠቃልሉ ‹‹የሚያስፈልገን በዘመን ላይ ተደርቦ ዘመንን የሚያድስ አዲስ ዘመን ነው።›› ብለዋል፡፡ አባባሉ መልካም ነው፤ ይሁንና በርዕሳቸው ‹‹የዘመን አዲስነት የጥርጣሬ ጥያቄ›› በስተመጨረሻው ‹‹አዲስ ዘመን›› የሚባል ነገር እንዳለ የሚያሳይ ሃሳብ ተሰንዝሮ ተደምድሟል፡፡
እኔ ወደዚህ የተቃርኖ ሃሳብ ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግም፤ ነገር ግን ለእኔ እንደታየኝና እንደማስበው ‹‹የዘመን አዲስም አሮጌም ያለ አይመስለኝም›› በሚል እሳቤ የግርማ ቦጋለን ሃሳብ እንደ መነሻ ይዤ የተወሰኑ ጉዳዮችን ለማንሳት ነው የፈለግሁት፤ እናም እንዲህ እቀጥላለሁ፡-
ዘመንን ስናስብ ጊዜ ነው ትዝ ሊለን የሚገባ። ጊዜ ደግሞ ሁሉንም ነገር የምናከናውንበት ከእኛነታችን ጋር ያለ ነገር ነው፡፡ በጊዜ ውስጥ ኖረን በጊዜ ውስጥ እናልፋለን፤ አዲስም ብንሆን እኛ ሰዎች ነን ‹‹በጨቅላነታችንና በወጣትነታችን›› ፤ አሮጌነትም የእኛ ነው ‹‹በእርጅና ዘመናችን›› እንጂ በጊዜ እና በዘመን ላይ የአሮጌነትም ሆነ የአዲስነት ታፔላ የመለጠፍ ነገር ብዙም የሚመቸኝ አይደለሁም፡፡ ያኔ ድሮ በአያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ስትወጣ የነበረችው ፀሐይ ዛሬም እሷ ናት እየወጣች እየገባች ያለችው። ጊዜና ዘመን አቆጣጠሩም ቢሆን ያው ነው፡፡
በእርግጥ ሰኞ ማክሰኞ ብለን ለቀናትና ለወራት መለያ ስም መስጠታችን ፤አዲስ እና አሮጌ ዓመት ማለታችን እርስ በእርስ ለመግባባትና ለመረዳዳት ይጠቅመን እንደሆነ እንጂ፤ በስተቀረስ ሁሉም ነገር ተጠቅልሎ ያለው እኛው አመለካከትና አስተሳሰባችን ውስጥ ነው፡፡ ለዘመንና ለቀናት አሮጌ እና አዲስ ማለት ግን ትርጉም ያለው ነገር አይመስልም፡፡
የአሮጌነትና የአዲስነት ጉዳይ የእኛው የሰዎች የአስተሳሰብ ጣጣ እንጂ ዓመታቱ ቀናቱና ወራቱ ያው ናቸው፡፡ በእጅ አይዳሰሱ፤በዐይን አይታዩ፤ በጆሮ አይሰሙ፤ በምላስ አይቀመሱ፤ ቀለምና ሽታ ወዘተ የላቸው፡፡ ዕሑድ ተጀምረው ቅዳሜ የሚያልቁት የሳምንቱ ቀናት፤ ያው የዓመቱ የዘመንና ዘመናቱ አካል ናቸው፤ እነርሱ እንደሆኑት፤ ዘመናቱም ናቸው፡፡ በደቂቃ እና በሰዓት እየተለኩ አንድ ረጅም ወደፊት የሚዘረጋ ማንነት ውስጥ ሆነው የሚጓዙ ፤ሰዎች ተወልደን አድገን ስናረጅና በሞት ስናልፍ፤ እነርሱ እዚያው በስፍራቸው ያሉ ፤ በአንድ አቅጣጫ የሚከንፉ መያዣ እና መጨበጫ የሌላቸው ሁነቶችና ክስተቶች ናቸው፡፡ አዲስም አሮጌም ያልሆኑ በመምሸትና በመንጋት፤መንኮራኩር ውስጥ ያሉ፡፡ የማያረጁ ነገር ግን የሚያስረጁ፤ ሮጠው የማይደክሙ ግን እኛን ሰዎችን እያሯሯጡ የሚያደክሙ ናቸው።
እንዲህ በሚሮጡ ቀናትና ዘመናት ፤በእነርሱ ሂደትና ቅይይር፤ በመምሸት እና መንጋት ሂደት ውስጥ ሰዎች ራሳችንን ልንቀይርና ልንለውጥ ካልቻልን ከቶም አዲስም ሆነ አሮጌ ያልሆኑት ዘመናትና ቀናት እኛን የመለወጥ አቅም የላቸውም፡፡ ስለ ለውጥ ሲታሰብ ምክንያት የሚሆነው ጉዳይ ዘመናቱና በዘመናቱ ውስጥ ያለው ነገረ- ሁነት ሳይሆን ለውጥን የሚሻ ማንነት በውስጡ ያለው ፍላጎቱና ሃሳቡ ነው ዋናው የመርከቡ ካፒቴንና መሪ፡፡ በሌላ አባባል በአስተሳሰባችን ያለው ነገር ፤ያው ማንነት ነው በተግባር ተተርጉሞ በገሀዱ ዓለም ሊከሰት ወይም ሊገለጥ የሚችለው፡፡
ስለዚህ ዘመናት በአሮጌነትም ሆነ በአዲስነት ስያሜ ብንሰይማቸው ከእያንዳንዳችን የመለወጥ እሳቤ እና ፍላጎት አንፃር የጎላ ሚና አላቸው ብሎ ለማለት ይከብዳል፡፡ ስለሆነም ይመሻል፤ ይነጋል፤ ቀናት፤ ወራትና ዓመታትም ዞረው ይመጣሉ ‹‹የሆነው ደግሞም የሚሆነው፤ የነበረውና ወደፊትም የሚኖረው፤ ያው በአንድ ማንነት ውስጥ ስለ ሁሉም ነገር ያለ አመለካከት ነው፡፡›› እሱ ነው ገዢው ሃሳብ፡፡ ከፀሐይ በታች እኛው ለእኛው ለውጥ እናመጣ ዘንድ ካልታተርን በስተቀር ሌላ አዲስም አሮጌም ካልሆኑት ዘመናት ጠብ የሚል ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
አዲስም አሮጌም ያልሆኑት ዘመናት የቀን ቆጠራ ውጤት እንጂ፤ የአዲስነትም ሆነ የአሮጌነት ቅመምና መልክ የላቸውም፡፡ የአምናው ማንነቱ ላይ በዘንድሮው ዓመት ያው ሆኖ ለውጥ ካልታየበት እከሌ እንቶኔ አዲስ እና አሮጌ ዓመት ቢል ምን ትርጉም አለው ? በዘመኑ ውስጥ ያለው ማንነት አዲስ እና አሮጌ ብሎ በሚቆጥረው ሰው ኑሮ ውስጥ አዲስነት ካልታዬና የነበረው እንደነበረ ከቀጠለ የዘመን መለዋወጥ ወይም አዲስ መሆን ያለመሆን ፋይዳ ያለው ነገር አይሆንም ብዬ አስባለሁ፡፡
በአንድ ዘመን ውስጥ ያለ ማንነት የዕድሜ ቀመር እየሠራ ከቀን ቀን ከወር ወር እያለና እየቆጠረ የባህርይና የድርጊት ለውጥ ሳያሳይ ዋዜማና ዓመት በዓል በማለት የአሮጌና አዲስ ዓመት መለከት ቢነፋ ፤ ‹‹የእንትን ምንቸት ግባ! የእንትን ምንቸት ውጣ !›› እያለ ቢለፍፍ፤ያምናው ኑሮና አሮጌ አመለካከቱ ግን አዲስ ነው። ባለው ዓመት እዚያው ከእርሱው ጋር ተጎልቶ ዐይኑን ቢያፈጥበት ይህ ትልቅ አሳዛኝና የሚያስተዛዝብ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡
አዲስም አሮጌም ያልሆኑት ዘመናት በጊዜና በሰዓትነታቸው የሚያስፈልጉን ለለውጥ ነው፡፡ ለአዲስ ሕይወትና ኑሮ ነው ብለን ካልን ፤ ዘመናቱን ለእነዚህ ዐቢይ ሁነቶች መዋጀት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ያለበለዚያ የለውጥ ማንነት ሽታ ያልዳሰሰው፤ ማንነት ይዞ፤ የአዲስ አሮጌ እሳቤና የዘልማድ ጉዞ ላይ ተሳፍሮና ተኮናትሮ መገኘት የትም አያደርስም የሚል ትሁት ግምት አለኝ፡፡
በመሆኑም እንደ ጋዜጠኛ ግርማ ቦጋለ አባባል ‹‹የዘመን አዲስም አሮጌም የለም» ብለን ብንልና በዚህ ብንስማማ፤ ወይም ‹‹ የዘመን አዲስ የለውም ›› በማለት ሃሳቡን ቅቡል ብናደርግና ‹‹የዘመን አዲስነት ሳይሆን፤ የሰው የኑሮ አዲስነት ፤የማህበረሰብ ብሎም የአገር የተለወጠና የተሻሻለ ማንነት አዲስነት፤ ብለን በየዓመቱ ብናቀነቅን የሚያሳምን የዘመን አዲስነት መገለጫ ይሆንልናል ብዬ አስባለሁ፡፡
‹‹ የዘመን አዲስነት›› ሳይሆን በቆጠሩት ዘመንና ወራት ውስጥ በአዲስነት የሚቆጠር ግለሰባዊም ሆነ ማህበራዊ ብሎም አገራዊ ለውጥ መፈጠሩና መታየቱ ነው ሊሰመርበት የሚገባ፡፡ በተፈጥሮ ያሉ ሣር እና ድንጋዩ ፤ አምናም ዘንድሮም ለውጥ የማይታይባቸው ሆነው ቢሆን እኛም ሰዎች መሰል ሁኔታ ቢንፀባረቅብን አዲስ እና አሮጌ ዓመት ማለታችን አይጠቅመንም፡፡
ከማይጠቅመን ነገር ጋር ተዛምደንና ተጣብቀን የምንከርም ከሆነ ደግሞ ‹‹ አሮጌ የምንለው ዘመን አወይቦን እርጅናን አልብሶ መሸምገላችን አይቀርም፡፡›› ስለዚህ ‹‹ አዲሱ ዓመት አሮጌው ዓመት ላይ እየተደረበ የአሮጌ ዘመንን ቁጥር ያሳድጋል ፤›› መባሉ እውነትነት አለውና በየዓመቱ ዘመንን ብቻ በራሱ አዲስ እያሉ መዘከሩ አስፈላጊነቱ ይህን ያህል አይደለም ማለት ነው፡፡
ደግሞም ‹‹ዘመንን አዲስ እና አሮጌ ማለት፤ በዘመን ላይ ማሳበብ፤ ወይ ዘመን!›› ማለት ከቶም መልስ የሚያስገኝ ነገር አይመስለኝም፡፡ ሁሉም ነገር ከዘመን ጋር ተያይዞ የሚወሳ ከሆነ ዕጣ ፈንታችን በሥራችን፤ በመውደቅና በመነሳታችን ሳይሆን በአሮጌና አዲስ ብለን በምንሰይማቸው ዘመናትና ቀናት መምጣትና መሄድ ውስጥ የሚወሰኑ መሆናቸው ነው፡፡
አዲስም አሮጌም ባልሆኑት ቀናት ወራትና ዓመታት የሰዎች ዕጣ ፈንታ አይወሰንም፡፡ በሥራቸው እንጂ፡፡ ስለዚህ ‹‹ የዘመን አዲስ አለው ? ›› ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ የሚሆነው ነገር በሰዎች ሕልውና ውስጥ ለውጥና አዲስ ነገር ከሆነ ዘመናቱ ሲለወጡ ለውጥ የሆነለት ማንነት አዲስ ዘመን ሊል የሚችልበት ዕድል ያለው መሰለኝ፡፡ የአዲስነት መገለጫ እና ፍሬ ከሕልው የሰው ማንነትና ኑሮ ውስጥ አንድ በአንድ ቆጥረን ማውጣት ከቻልን የማንነትና የአኗኗር ፤ የለውጥና የተሐድሶ ትሩፋት በእጅ ከተዳሰሰ፤ በዐይን ከታየ ፤ ያኔ ሁልቀን አዲስ ዘመን፤በየዕለቱ አዲስ ለውጥ ማለትን የሚከለክለን ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
ስለዚህ የዘወትር ጥያቄ ሆኖ ሊነሳ የሚገባው ነገረ-ጉዳይ የዕድሜያችንን ቁጥር እያበዛ ሸምግሎ የሚያሸመግለንን ሮጦ መጥቶ ሮጦ የሚሄደውን ዘመን መቁጠር ሳይሆን በዓመቱ ውስጥ ባሉ በእያንዳንዱ ቀናት ለውጥ እና አዲስ ነገር እየናፈቀን ለአዲስ ኑሮ እና ሕይወት አምርረን መታገላችን ነው ዋናው ነገር፡፡
በእርግጥ ‹‹ነገም ሌላ ቀን ነው !›› ነገ በሚሆነው ነገር ለመመካት ብዙም የሚበረታታ ሃሳብ ባይሆንም ለነገ እያሰቡ ስለ ለውጥ፤ ተሀድሶ፤ስለ አዲስ ሕይወትና ዘመን ፤መሥራቱ በእጅጉ የሚደገፍ ነገረ- ሃሳብ ነው ፡፡ ደግሞም አዲስ እና የተለየ፤ጠቃሚና አስፈላጊ የዕድገትና የብልጽግና የተሻለ ቀንና ብሩህ ሕይወትን ለማስረፅ መንቀሳቀሰ ይጠበቅብናል። ያኔ ከዘመን ቆጠራ ባለሀብትነት ይልቅ፤ የአኗኗር አዲስ ማንነትና ሁነት ፍንትው ብሎ ይገለጥና የእኛ ይሆናል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡
በተረፈ በሌላ ነገረ-ሃሳብ ላይ ብቅ እስከምል ድረስ ለሁላችንም ብዙ ሰላም ተመኘሁ ሰላም!!!
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ